2 Kings 20

የሕዝቅያስ መታመም

20፥1-11 ተጓ ምብ – 2ዜና 32፥24-26፤ ኢሳ 38፥1-8 1በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር። የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እርሱ ሄዶ፣ “እግዚአብሔር፣ ‘ትሞታለህ፤ ከእንግዲህ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል’ ብሎሃል” አለው።

2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ 3እግዚአብሔር ሆይ፤ በታማኝነትና በፍጹም ልብ በፊትህ እንደ ሄድሁ፣ አንተን ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ዐስብ፤” ሕዝቅያስም ምርር ብሎ አለቀሰ።

4ኢሳይያስ የመካከለኛውን አደባባይ ዐልፎ ከመሄዱ በፊት የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እርሱ መጣ፤ 5“ተመለስና የሕዝቤን አለቃ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፤ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፤ እፈውስሃለሁ። ከዛሬ ሦስት ቀን በኋላ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ትወጣለህ፤ 6በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ እኔ ስለ ራሴና ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል ይህችን ከተማ እከላከልላታለሁ።’ ”

7ከዚያም ኢሳይያስ፣ “ትኵስ የበለስ ጥፍጥፍ አዘጋጁ” አላቸው፤ እነርሱም አዘጋጅተው ዕባጩ ላይ አደረጉለት፤ ተፈወሰም።

8ሕዝቅያስም፣ “እግዚአብሔር እኔን ስለ መፈወሱ፣ ከሦስት ቀን በኋላም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስለ መውጣቴ ምልክቱ ምንድን ነው?” ሲል ኢሳይያስን ጠየቀው።

9ኢሳይያስም፣ “እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም ምልክቱ ይህ ነው፤ ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት ይቅደምን? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ?” ሲል ጠየቀው።

10ሕዝቅያስም መልሶ፣ “ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት መሄዱ ቀላል ነገር ነው፤ ይልቁን ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ” አለ።

11ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም አካዝ በሠራው ደረጃ ላይ የወረደውን ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላው እንዲመለስ አደረገ።

ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች

20፥12-19 ተጓ ምብ – ኢሳ 39፥1-8 20፥20-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 32፥32-33 12በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን የሕዝቅያስን መታመም ሰምቶ ስለ ነበር፣ ደብዳቤና ገጸ በረከት ለሕዝቅያስ ላከለት። 13ሕዝቅያስም መልክተኞቹን ተቀብሎ በዕቃ ቤቱ ያለውን ሁሉ ብሩን፣ ወርቁን ቅመማ ቅመሙንና ከፍ ያለ ዋጋ ያለውን ዘይት የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱንና በቀረውም ግምጃ ቤት ያለውን በሙሉ አሳያቸው። በቤተ መንግሥቱም ሆነ በመላው ግዛቱ ሕዝቅያስ ሳያሳያቸው የቀረ ምንም ነገር አልነበረም።

14ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ሕዝቅያስ ሄዶ፣ “እነዚያ ሰዎች ምን አሉህ? የመጡትስ ከወዴት ነው?” ሲል ጠየቀው።

ሕዝቅያስም መልሶ፣ “የመጡት ከሩቅ አገር ከባቢሎን ነው” አለው።

15ነቢዩም፣ “በቤተ መንግሥትህ ምን ምን አዩ?” ሲል ጠየቀው።

ሕዝቅያስም፣ “በቤተ መንግሥቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በግምጃ ቤቶቼ ሳላሳያቸው የቀረ ምንም ነገር የለም” አለ።

16ከዚያም ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ 17በቤተ መንግሥትህ ያለው ሁሉ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት በሙሉ ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ጊዜ በርግጥ ይመጣል፤ አንዳች የሚቀር ነገር የለም ይላል እግዚአብሔር 18የሥጋህ ቍራጭ የዐጥንትህ ፍላጭ ከሚሆኑት፣ ከምትወልዳቸው ልጆችህ አንዳንዶቹ በምርኮ ይወሰዳሉ፤ በባቢሎንም ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ይሆናሉ።” 19ሕዝቅያስም፣ “የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው” ሲል መለሰ፤ “እኔ እስካለሁ ድረስ ሰላምና ጸጥታ ከተገኘ የሆነው ይሁን” ብሎ አስቧልና። 20በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ ኵሬውንና ውሃውን ወደ ከተማዪቱ ያመጣበትን የመሬት ለመሬት ቦይ እንዴት አድርጎ እንደ ሠራው በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 21ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ምናሴም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

Copyright information for AmhNASV